Jack-Adam-Staff-Illustrator-open-letter-anonymous-1024x848

የግል አስተያየት:- ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የተጻፈ ግልጽ ደብዳቤ

ይህ አጭር የግል አስተያየት የኢትዮጵያ ምህዳሮች የኢትዮጵያውያን ሴቶችን እና ሴት ልጆችን ድምጽ እና አመለካከት ያካተቱ መሆናቸውን የሚያረጋግጡ ሰፊ ውይይቶችን ለማስጀመር ታስቦ የተጻፈ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በትረ-ሥልጣኑን ሲረከቡ ባደረጉት ንግግር መሰረት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የጻፍነው ግልጽ ደብዳቤ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ፍትሕን ለማግኘት የሚያደርጉት ተጋድሎ መጠነ-ሰፊ ውጤት እንዲኖረው ለማስቻል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕውቅና እንዲሰጡት የሚያበረታታም ነው።

====================================================================== 

የተከበሩ ዶ/ር አብይ አህመድ አሊ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር፣

 

ከሁሉ አስቀድመን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ስለበቁ በዚህ አጋጣሚ እንኳን ደስ አለዎት ልንልዎ እንወዳለን። እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሁሉ ፈዋሽ የሆነውን የመጀመሪያ ንግግርዎን ስናዳምጥ የተናገሩት እያንዳንዱ ቃል ልባችንን ሰርስሮ ገብቷል። እኛም ሆንን መላው የአገሪቱ ህዝብ በንግግርዎ ውስጥ የገለጿቸው ሀሳቦች ዕውን እንዲሆኑ ከልባችን እንመኛለን። አስተዳደርዎ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚያስጀምር እንዲሆን የሚያስፈልግዎትን መልካም ፍቃድ እና ድጋፍ በዙሪያዎ እንደሚያገኙም ከልባችን ተስፋ እናደርጋለን።   

 

ክቡርነትዎ፣

 

ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመን በኢትዮጵያ ውስጥ የጾታ እኩልነትን ዕውን ለማድረግ በመስራት ላይ ለምንገኝ ሰዎች ከፍተኛ ቦታ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች አጽንኦት ሰጥተን ልናነሳ እንወዳለን። ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የኢትዮጵያ ሴቶች ፍትሕን ለማግኘት ለሚያደርጉት ትግል ዕውቅና መስጠትዎን እና በዚህ ረገድ ይበልጥ መሰራት እንዳለበት መግለጽዎን ከልብ እያደነቅን፤ በአሁኑ ወቅት እንዲሁም ከዚህ ቀደም በነበረን ታሪክ ውስጥ የኢትዮጵያ ሴቶች ለተጫወቱት ዘርፈ ብዙ እና ቁልፍ ሚና እርስዎም ሆኑ አስተዳደርዎ ዕውቅና መስጠታችሁ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነም በአጽንኦት እንገልጻለን። እንዲህ ያለ ዕውቅና መሰጠቱ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የጾታ እኩልነትን እና ማህበራዊ ፍትሕን ዕውን ለማድረግ እና ለማስፋፋት ሲሰሩ የነበሩና በመስራት ላይ የሚገኙ ሴቶችን እና ወንዶችን የሚያበረታታ እና የሚያነሳሳ እንደሚሆን ጽኑ እምነት አለን። ምንም እንኳን እነዚህ ችግሮች መፈታታቸው የኢትዮጵያ ሴቶችን ህይወት ለማሻሻል ወሳኝ ቢሆንም፣ የትኛውም ጾታ ከሌላኛው ተነጥሎ መኖር እንደማይችል እንገነዘባለን። ስለሆነም፣ ኢትዮጵያውያን ወንዶች ወደ ጾታ እኩልነት በሚደረገው ጉዞ ውስጥ ለሚጫወቱት ሚናም እንዲሁ ዕውቅና መስጠት አስፈላጊ ነው።

 

ይህ እንዳለ ሆኖ፣ ጉልህ እና ዘላቂ የሆነ ለውጥ ለማምጣት በከፍተኛ የአመራር ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎችን የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማግኘት ወሳኝ ነው። እስከዛሬ ድረስ የተሰሩ ስራዎች የሴቶች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጥቅሞች በፖሊሲ ደረጃ እንዲጸባረቁ ያደረጉ ቢሆንም፤ በገጠርም ሆነ በከተማ በሚገኙ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ህይወት ውስጥ በግልጽ የሚታይ ስር-ነቀል ለውጥ በማምጣት ረገድ ግን ያደረግነው እርምጃ የቀንድ አውጣ ጉዞ ሊባል የሚችል ነው። እርግጥ ነው ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ኢኮኖሚ ጋር በሂደት እየተቀናጀች መምጣቷ ለኢትዮጵያ ሴቶች አዳዲስ ዕድሎችን ፈጥሯል። ከዚህ ጎን ለጎን፣ የጾታ እኩልነት ንቃትን እና እርምጃዎችን በተመለከተ ተጨማሪ ስራዎች እንዲሰሩ የሚጠይቁ አዳዲስ ጥያቄዎችን እና ተግዳሮቶችንም እንዲሁ ይዞ መጥቷል።

 

አስተዳደርዎ የውይይት መድረኮች መፍጠርን በመደገፍ ረገድ የሚመራ ይሆናል በሚል ተስፋ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ፍትሕ ማግኘታቸውን ከማረጋገጥ እና የጾታ እኩልነትን ከማስፋፋት ጋር በተያያዘ ስናስብባቸው የቆዩትን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ልናካፍልዎ እንወዳለን። ይህንን ስንጽፍልዎት፣ በጋራ በመሆን ወሳኝ ጥያቄዎችን በማንሳት እርስዎም ሆኑ አስተዳደርዎ ተቀናጅቶ በመስራት ትርጉም የሚሰጡ መልሶች ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት ለመደገፍ እንችላለን በሚል ተስፋ ነው።

  1. የኢትዮጵያ ሴቶች ፍላጎቶች እና ጥያቄዎች ቁልፍ በሆኑ የፖለቲካ ሂደቶች እና ተቋማት ውስጥ ትርጉም ባለው መልኩ መወከል የሚችሉት እንዴት ነው? የፖለቲካ መድረኮች አብዛኛውን ጊዜ ፍርሃትን በሚያጭሩበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ሴቶች በፖለቲካ ውስጥ ያላቸውን ድምጽ እና ተሳትፎ ማጎልበት የምንችለው በምን መልኩ ነው?
  2. አስተዳደርዎ፣ በርካታ ሴቶችን ከጥቃቅን እና አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት ጥላ ስር አውጥቶ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ወደ መሆን እና ሐብትን ወደመፍጠር ሊያሸጋግሩ የሚችሉ ምን ዓይነት ስራዎችን በግምባር ቀደምነት ሊመራ ይችላል?
  3. አሁንም ድረስ በሴቶች እና በወንዶች መካከል ያለውን ግንኙነት፣ የስራ ክፍፍል እና ተደራሽነት ከችሎታ ይልቅ ጾታን መሰረት በማድረግ የሚወስኑ ጨቋኝ የሥርዓተ-ጾታ እና ማህበራዊ አስተሳሰቦችን አስተዳደርዎ መጋፈጥ የሚችለው በምን መልኩ ነው?
  4. አስተዳደርዎ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ወንዶች እና ሴቶች የሥርዓተ-ጾታ ፍትሕ ምቹ ሁኔታን መፍጠር የሚችለው እንዴት ነው? ኢትዮጵያውን ሴቶች እና ሴት ልጆች በሙሉ በሁሉም ዓይነት የህይወት ገጽታዎች ውስጥ ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ መሳተፋቸውን እና በመላው ኢትዮጵያ ውስጥ ካለምንም ፍርሃት ሙሉ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ተሳትፎ ማድረግ መቻላቸውን አስተዳደርዎ በምን መልኩ ማረጋገጥ ይችላል?

 

እነዚህ አራት ጥያቄዎች በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ምህዳሮች ውስጥ ያለውን የሥርዓተ-ጾታ አጀንዳ ዝርዝር ጉዳዮች ጠለቅ ባለ መልኩ ለመመርመር ቁልፍ መነሻ ነጥቦች ናቸው ብለን እናምናለን።

 

ከፊትዎ የሚጠብቁዎትን በርካታ ሥራዎች ሙሉ በሙሉ የምናውናቅና በሥራ ላይ ባሳለፏቸው ጥቂት ቀናት ውስጥ የወሰዷቸውን ጉልህ እርምጃዎች የምንገነዘብ ሲሆን እርስዎ እና አስተዳደርዎ መሻሻልን እና ሥር-ነቀል ለውጥን ለማምጣት የምትሰሩት ሥራ በሥርዓተ-ጾታ መነጽር በሚገባ የተፈተሸ እና የተመረመረ እንዲሆን እንጋብዛለን። በሃገራችን ውስጥ ከሚደረጉ በርካታ የውይይት መድረኮች ለመረዳት እንደሚቻለው በርካቶች የጾታ እኩልነትን የሚረዱት የቁጥር ጨዋታ አድርገው እንደሆነ እና የሴቶችን ተዋጽኦ በመጨመር ላይ ብቻ የተመሰረተ መሆኑን እና እነዚህ አካሄዶች በጾታ እኩልነት አጀንዳ ላይም ሆነ በሴቶች ህይወት ላይ ሥር-ነቀል ለውጦችን ለማምጣት ያደረጉት አስተዋጽኦ በጣም አነስተኛ መሆኑን ለመረዳት ይቻላል።

 

የጾታ እኩልነት ለብቻው ተነጥሎ ሊስተናገድ የማይችል የማህበራዊ ፍትሕ ጉዳይ መሆኑን በተግባር ያሳዩናል ብለን የምንጠብቅ ሲሆን፤ በዚህ ረገድ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መድረኮች ውስጥ የሴቶችን ፍላጎት በሚያንጸባርቁ አስተሳሰቦች፣ ፖሊሲዎች፣ ተቋማት እና የአፈጻጸም ዘዴዎች መካከል ያለውን መሰረታዊ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ መዳሰስ ይኖርብናል።

 

ምንም እንኳን የኢትዮጵያውያን ሴቶች ተጋድሎ እና ድል በርካታ ቢሆንም እና ይህም በምንኖርባት ዓለም ውስጥ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ቀጣይ በሆነ የለውጥ ሂደት ውስጥ የሚያልፍ ቢሆንም የሥርዓተ-ጾታ ፍትሕን ለማረጋገጥ ያለዎትን ቁርጠኝነት በፈጣን መንገድ ለማስኬድ አቀጣጣይ ይሆናሉ ብለን የምናምናቸውን ወሳኝ መሳሪያዎች አጽንኦት ሰጥተን ለመጥቀስ እንወዳለን።  

 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥርዓተ-ጾታ አማካሪ ቡድን

 

በአገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ የጾታ እኩልነትን እና የሥርዓተ-ጾታ ፍትሕን ለማስፋፋት የሚሰሩ ወንዶችን እና ሴቶችን ያካተተ እና ተቀዳሚ ስራው ከኢትዮጵያ ፍላጎቶች እና ዓላማዎች ጋር የሚጣጣም ስር-ነቀል ለውጥ የሚያመጣ የሥርዓተ-ጾታ አጀንዳ ዙሪያ ለእርስዎ መረጃ መስጠት እና ማማከር የሆነ ብሔራዊ የአማካሪ ቡድን ያቋቁሙ።

 

50-50 ካቢኔ

 

በዓለማችን ውስጥ ባሉ ሃያላን ሃገራት ውስጥ ተመጣጣኝ የጾታ ተዋጽኦ ያለው ካቢኔ መደበኛ እና የተለመደ እየሆነ የመጣ ሲሆን እርስዎም ይህንኑ የአመራር ዘይቤ እንዲከተሉ እናበረታታለን። ሆኖም ግን፣ የዚህ ካቢኔ አወቃቀር ከዚህ በፊት “በወንዶች ይዞታ” ስር የነበሩ የኃላፊነት ቦታዎች፤ ማለትም፣ የውጭ ጉዳይ፣ የንግድ፣ ኢንዱስትሪ፣ ፋይናንስ እና መከላከያ፤ ወደ ኢትዮጵያውያን ሴቶች የእውነት መሸጋገራቸውን የሚያንጸባርቅ እንዲሆን አጥብቀን እንጠይቃለን። ለእነዚህ የኃላፊነት ቦታዎች ሴቶችን የመምረጥ ሂደቱ ለኢትዮጵያውያን በሙሉ ማህበራዊ ፍትሕን ለማረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነትም እንዲሁ የሚያንጸባርቅ መሆን አለበት።

 

የሴቶች መብት ተከራካሪዎች መድረክ

 

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ አመራርዎ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማዳረሱን ተመልክተናል። በመሆኑም፣ በገጠርም ሆነ በከተማ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ፍላጎቶች እና መብቶች በማቀንቀን እንዲሁም በግልጽ በማስቀመጥ ረገድ ግንባር ቀደም ሚና ሲጫወቱ የቆዩ ኢትዮጵያውያን የሴቶች መብት እና የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎችን በመሰብሰብ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚሰጡትን ሃሳብ የማዳመጥ ባህልዎን እንዲገፉበት እናበረታታለን። ኢትዮጵያውያን ሴቶች ሲባል አንድ ዓይነት ስብስብ ባለመሆናቸው ይህ መድረክ ልዩነታችን የሚያንጸባርቅ እንዲሆን እናበረታታለን።

 

 

የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት ሕግ

 

ሲቪል ማህበራት መንግስት ዴምክራሲን ለማስረጽ የሚያደርገውን ጥረት እንዲያሳከ በመደገፍ ረገድ ያላቸው ሚና የሚናቅ አይደለም። በ2001 ዓ.ም የወጣው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት አዋጅ በጾታ እኩልነት ዙሪያ ሲደረጉ የነበሩ ውይይቶችን እና ግንዛቤዎችን ወደ ኋላ በመመለስ ረገድ የፈጠረው ተጽዕኖ በግልጽ የሚስተዋል ነው። የሴቶች መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ግንዛቤ በመፍጠር እንዲሁም አገልግሎቶችን በመስጠት አስተዳደርዎን እንዲደግፉ በሚያስችል መልኩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት አዋጁን እንዲያሻሽሉ እናበረታታለን።

 

 

ሥርዓተ-ጾታን ያገናዘበ የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ

 

ኢትዮጵያ በፈጣን የኢንዱስትሪ አብዮት ውስጥ በማለፍ ላይ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ፤ በርካታ ሴቶች ኢ-መደበኛ ከሆነው ዘርፍ ወደ መደበኛው ዘርፍ ለመሸጋገር ያላቸው ዕድል በማበብ ላይ ይገኛል። ሆኖም ግን፣ በሌሎች በርካታ ታዳጊ አገሮች ውስጥ እንዳስተዋልነው ዜጎችን ያላማከለ የኢንዱስትሪ ልማት አሉታዊ ውጤቶችን የሚያስከትል ሲሆን፤ በዚህ አጋጣሚ ከዚህ ጋር በተያያዘ ያለንን ስጋት ለመግለጽ እንወዳለን። በኢንዱስትሪ ልማት አማካኝነት የተፈጠረውን የስራ ዕድል ተጠቅመው በርካታ ሴቶች ወደ ገበያው ከመቀላቀላቸው ጎን ለጎን ጾታን ያገናዘቡ ግቦችን በማስቀመጥ ይህ ፖሊሲ ይበልጥ እንዲበለጽግ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። በኢንዱስትሪ ውስጥ ተሰማርተው ለሚገኙ ሴቶች በተለይ አሳሳቢ የሆኑት ጉዳዮች ከወንዶች እኩል ክፍያ ማግኘት፣ ከወሲባዊ ትንኮሳ ነጻ መሆን፣ የሕጻናት እንክብካቤን ጨምሮ ነገር ግን በዚያ ብቻ ሳይወሰን፣ ተለዋዋጭ ለሆነው የህይወታቸው ገጽታ ተስማሚ የሆኑ መረጃዎች እና አገልግሎቶች ተደራሽነት ናቸው።

 

ብሔራዊ የወሲባዊ ትንኮሳ ሕግ እና ማስከበሪያ ዘዴዎች

 

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሴቶች በማህበራዊ ሆነ በግል ሕይወት ውስጥ በየእለቱ የሚገጥማቸውን የወሲባዊ ትንኮሳ መጠን ችላ ልንለው አንችልም። የወሲባዊ ትንኮሳ ሕጎች አስፈላጊነት በተለይም ደግሞ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ እጅግ ወሳኝ ሲሆኑ የሕግ ማስከበሪያ እና የፍርድ አሰጣጥ ዘዴዎችም በግልጽ መቀመጥ አለባቸው። የሦሰት ሴት ልጆች አባት እንደመሆንዎ እርስዎ የሚመሩት መንግስት በአገር አቀፍ ደረጃ ወሲባዊ ትንኮሳን በምንም አይነት መልኩ የማይታገስ ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

 

የሴቶች እና ሕጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር ሪፎርም

 

የጾታ እኩልነት አስተሳሰብን በመፍጠር ረገድ የሴቶች እና ሕጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር እና በክልል ደረጃ ያሉ ተጓዳኝ አደረጃጀቶች ያላቸው ውጤታማነት እንዲገመገም አጥብቀን እንጠይቃለን። ሴቶችን ማብቃት ከሚለው ንግግር ባለፈ፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና ተጓዳኝ የክልል አደረጃጀቶች በጾታ ዙሪያ የተቃኘውን የኢትዮጵያ ሴቶች ህይወት በመፈተሽ ረገድ ምን ያህል ውጤታማ ሆነዋል? በጾታ እኩልነት ዙሪያ የተሰሩ ስራዎችን “የሴቶች ጉዳይ” ብቻ ተደርገው ከመታየት ጋር ምን ያህል አላቋል? በተመሳሳይም፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሕጻናትን ጉዳይ በበላይነት እንዲመራ መደረጉ ውጤታማ ተቋም የመሆን አቅሙን የሚያሳሳ ሊሆን ይችላል። ከጊዜ ወደ ጊዜ በመፈጠር ላይ ያሉ የኢትዮጵያውያን ሴቶች ፍላጎቶችን በማስተናገድ ረገድ እንዲሁም በማህበረሰብ ውስጥ ያለውን የተዛባ ሚዛን በማስተካከል ረገድ ያለውን ውጤታማነት ለማሻሻል ሲባል፣ አስተዳደርዎ የሴቶች እና ሕጻናት ጉዳይ ሚኒስቴርን ወደ ሥርዓተ-ጾታ ሚኒስቴር በአፋጣኝ እንዲለውጥ ሃሳብ እናቀርባለን። በእውነትም፣ እስካሁን የተሰሩትን እና በሂደት ላይ ያሉትን ስራዎች የሚያጠናክሩ ጉልህ ሽግግሮችን ለማየት የምንፈልግ ከሆነ፤ ሴቶችን ከማብቃት እና ስር-ነቀል ማህበራዊ ለውጦችን ለማምጣት ከሚሰራው ስራ ጋር በኢትዮጵያ ውስጥ አሉታዊ የወንድነት አመለካከቶችን ለመለወጥ የሚሰሩ ስራዎች እንዲቀናጁ አጥብቀን እንጠይቃለን። በዚህ የመሻሻል ሂደት ውስጥ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና በትምህርት ሚኒስቴር መካከል የቅርብ ትስስር በመፍጠር የትምህርት ሥርዓት ማሻሻያ በማድረግ ስርዓተ ጾታን ያገናዘቡ አስተሳሰቦችን እና እሴቶችን ማካተት ላይ ሊሰራ ይገባል።

 

ለምርምር ስራ ከፌዴራል መንግስት የሚመደብ የገንዘብ ድጋፍ

 

በመጨረሻም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የጾታ እኩልነት ሁኔታ የሚያጠናቅር እና ለፖሊሲ ቀረጻ ግብዓት የሚሆን መረጃ የሚሰጥ መጠነ-ሰፊ እና ስር-ነቀል አገር አቀፍ ጥናት ማከናወን አስፈላጊ መሆኑን ልናሰምርበት እንወዳለን። ለኢትዮጵያውያን ሴቶች ፍትሕን ለማምጣት ያለዎትን ቁርጠኝነት ወደ ተግባር ለመለወጥ እንዲህ አይነቱን ምርመር ለማከናወን ከፌዴራል መንግስት የሚመደብ የገንዘብ ድጋፍ ወሳኝ ነው።

 

ክቡርነትዎ፣

 

የእነዚህ ወሳኝ እርምጃዎች ግንባር ቀደም አቀንቃኝ እንደሚሆኑ እና የጾታ እኩልነት ጉዳይ የሴቶች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን እውነተኛውን የኢትዮጵያ ሕዳሴ የሚመራ የማህበራዊ ፍትሕ እና ተሳትፎ ጉዳይ መሆኑን አጉልተው እንደሚያሳዩ በተስፋ እንጠብቃለን።በተጨማሪም፣ በአሁኑ ወቅት ያለውን የአንድነት እና የሠላም መንፈስ እያደነቅን፣ በእነዚህ ሂደቶች ውስጥ የሴቶች እና የሴት ልጆች ሙሉ ተሳትፎ እና አመራር አስፈላጊ መሆኑን ልናሰምርበት እንወዳለን።

 

ይህን ጉዳይ እንዲሁም ከላይ ያቀረብናቸውን ምክረ-ሐሳቦች እርስዎ እና አስተዳደርዎ ከግምት ውስጥ እንዲያስገቧቸው አጥብቀን ስንጠይቅ፤ በታላቅ ተስፋ ነው።

 

ከአክብሮት ጋር፣

 

ቢልለኔ ስዩም ወልደየስ እና ሠዊት ኃይለሥላሴ ታደሠ

 

ትርጉም፡- ፅኑ ዓምደሥላሴ ወርቁ

Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *